በጽንፈኝነት ሥም
በቅድሚያ ግን አንድ ጥያቄ ላንሳና ሀሳቤን ልጀምር፡፡ መንግስት ጽንፈኝነትን አምርሮ ለመታገል የግዴታ የታዋቂ አመራሮች ደም መፍሰስ
አለበት ነው? ይህ መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ የአቶ ግርማን ሞት ተከትሎ
በርካታ ፉከራ ከመንግስት እየተሰማ ነው፡፡ መንግስት ‹‹ከዚህ በኃላ››
ህግን ለማስከበር ወደኃላ እንደማይል በመደስኮር ላይ ይገኛል፡፡ ቆይ አቶ ግርማ ከመሞታቸው በፊት መንግስት ህግን ለማስከበር አምርሮ
እንዲታገል የሚያስችል አሳፋሪ ስራ በዚች ሀገር ላይ እየተሰራ አልነበረም ማለት ነው? አቶ ግርማ ባይሞቱ ኖሮ ይህን ፉከራቸውን
አንሰማውም ነበር ማለት ነው? ቁርጠኝነታቸውን ለማሳየት ለምን የሰዎችን ሞት መጠበቅ አስፈለገ? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡
የአማራ ክልል መንግስት በበኩሉ ከዚህ በኃላ ህገወጥ አሰራርን እንደማይታስና
ጽንፈኝነትን እንደሚታገል መግለጫ አውጥቷል፡፡ ቆይ ያልገባኝ ነገር
ከአቶ ግርማ መገደል በፊት በአማራ ክልል መንግስት እይታ ይች ሀገር የህግ የበላይነት የሰፈነባት፣ ሰዎች በሰላም የሚኖሩባት ሀገር
ነበረች ማለት ማለት ነው? እነዚህ ሀሳቦች መሰረታዊ ናቸው፡፡
የግለሰቦች ሞትን እንደ ህጋዊ ሽፋን በመጠቀም መንግስት የራሱን አላማ
ለማሳካት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ይችን ሀገር የሚጠቅም ነው ተብሎ አይታሰብም፡፡ እጃቸው በደም የተጨማለቁ ሰዎች በአደባባይ በሚሸለሙበት
ሀገር ስለ ሀገራቸው ሲሉ መንግስትን በሀሳብ የሚሞግቱ ሰዎችን አሸባሪ በሚል ታርጋ ማሳደድ ለዚች ሀገር የሚፈይደው ነገር አይኖርም፡፡
አሁን ባለንበት ሁኔታ ሀሳብን ቁጥር አንድ እየፈራ ያለው መንግስት ብቻ ነው፡፡ ማህበረሰቡን በተለያየ ነገር እያደናገሩ እውነታውን
እንዳይረዳ ማድረግ እንደ አጀንዳ ተይዞ በሚሰራበት ሀገር እውነትን የሚገልጡ ሀቀኛ ሰዎች በመንግስት ዘንድ ቦታ አይኖራቸውም፡፡
የተለያየ ታርጋ እየለጠፉ ሀቀኛ ሰዎችን ማሳደድ ከህወአት የወረስነው ካንሰራችን ነው፡፡ ይህ መንግስታዊ ባህላችን የት ሊያደርሰን
እንደሚችል ግልጽ አይደለም፡፡
የራሱ ብልሹ አሰራር የሚያስደነግጠው መንግስት ኢንተርኔትን ሆን ብሎ
በመዝጋትና አቅሙን በማዳከም ማህበረሰቡ ተገቢውን መረጃ እንዳያገኝም እያደረገ ነው፡፡ በራሱ የሚተማመን መንግስት ኢንተርኔትን ፈጽሚ
ሊዘጋ አይችልም፡፡ ሀሳብን በነጻነት መግለጽ ህገ መንግስታዊ መብት ነው፡፡ መንግስትን በሀሳብ መሞገት ህዝብን ለሽብር ማነሳሳት
ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ መንግስት ህግን እያስከበረ እንዳልሆነ መተንተን ሽብርን ማነሳሳት የሚል ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡
በእርግጥ በሀገራችን አሁን ምን እየተካሄደ እንዳለ እውነታው የተገለጠላቸው
ሰዎች በጣም ጥቂቶች በሆኑበት ሁኔታ የሚፈለገው ለውጥ ይመጣል ተብሎ አይታሰብም፡፡ መንግስት በሳል ማህበራዊ አንቂዎችን የሚጠላበት
አንዱ ምክንያት እውነትን እየገለጡ ማህበረሰቡን ከተኛበት ስለሚቀሰቅሱ ብቻ ነው፡፡ አይን ገላጭ ማህበራዊ አንቂዎች መንግስት አምርሮ
የሚጠላቸው የህብረሰተብ ክፍሎች ናቸው፡፡ አንድ ውኃ የሚያነሳ እርምጃ
በወንጀለኞች ላይ ወስዶ የማያሳየን መንግስት በየቀኑ የፓርኮችን ምርቃት ያስኮመኩመናል፡፡ ሲፈልጉ ጎርጎራ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ኮይሻ
ፕሮጀክት በሚል ማደናገሪያ አጀንዳ ዛሬም ህዝብ እየሰበሰቡ ለራሳቸው እያስጨበጨቡ ይገኛሉ፡፡ አሁን በአይን በሚታይና አብለጭላጭ
በሆኑ ነገሮች በርካታ ሰው እየተሸደ እንደሆነ እሙን ነው፡፡
ውስጤ አንድ ነገር ይነግረኛል፡፡ ጊዜ ሊወስድ ቢችልም በዚችልም በዚች ሀገር አንድ ያልተጠበቀ ነገር እንደሚከሰትና የፖለቲካው ሁኔታ እንደሚለወጥ አመናለሁ፡፡ ይህ ክስተት መንግስትንም ሆነ ማህበረሰቡን የሚያስተምር ይሆናል ብየ አስባለሁ፡፡ ይህ በማን ነው የሚሆነው ከተባለ መልሱ ቀላል ነው፡፡ ይህነ አድራጊው ፈጣሪ ነው፡፡


Comments
Post a Comment