በሞት አፋፍ ላይ ያለው የሀገራችን የፕሬስ ነጻነት

 









የፕሬስ ቀን በመላው ዓለም ተከብሮ እንዲውል ለመጀመሪያ ጊዜ የተወሰነው በዩኒስኮ በ1991 (እ.ኤ.አ) ሲሆን ይህም አላማውም በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰውን ጥቃትና እንግልት ለመከላከል ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡ በዚህ መሰረት የዓለም የፕሬስ ቀን በየዓመቱ ሚያዚያ 25 ቀን ተከብሮ ይውላል፡፡

ዘንድሮም የዓለም የፕሬስ ቀን ሚያዚያ 25 ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ30ኛ ጊዜ ‹‹ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መከበር ለሌሎች ሰብአዊ መብቶች መከበር›› በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ውሏል፡፡ ቀኑ በሀገራችንም በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ እንደዋለ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በሀገራችንም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ከዩኔስኮና ከመብቶችና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል ጋር በመተባበር ቀኑን በውይይት መድረክ አስቦት ውሏል፡፡ በመድረኩ ላይ እንደተገለጸው  አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የፕሬስ ነጻነት አደጋ ውስጥ ገብቷል ነው የተባለው፡፡ የጋዜጠኞች መታሰርና እንግልት እየጨመረ እንደመጣም የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በመድረኩ ላይ አስታውቋል፡፡

ሌላው በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ለማህበረሰቡ መረጃ የሚሰጡ የማህበራዊ እንደ ዩቲዩብ፣ ቴሌግራምና ፌስቡክ ያሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች እንዲዘጉ መደረጉ የሰዎችን መረጃ የማግኘት መብት እንደገደበውም ነው የተገለጸው፡፡

በሀገራችን ህገ መንግስትም ሆነ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ መሰረት ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሀሳብ በነጻነት የመያዝና የመግለጽ እንዲሁም መረጃ የመጠየቅ የማግኘትና የማስተላለፍ መብት የተከበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እነዚህ የሰዎች መብቶች እየተጣሱ እንደሆነ በሀገራችንም ሆነ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚወጡ ሪፖርቶች ያስገነዝባሉ፡፡

የፕሬስ ቀን ሲከበር የሰዎች መረጃ የማግኘትና የማስተላለፍ መብት መከበር እንዳለበትም አብሮ ይዳሰሳል፡፡ በሀገራችንም ይህን የሰዎችን መብት የሚያከብሩ ተቋማት የሉም ባይባልም ከመንግስት ተቋም መረጃ ጠይቆ በነጻነት ማግኘት ግን አሁንም ቢሆን በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚመነጨው ህጉን ካለማወቅና ከግንዛቤ ማነስ ብቻ ሳይሆን ህጉን ጠንቅቀው እያወቁም ሆን ብለው የሰዎችን የመረጃ የማግኘት መብት የሚደፈጥጡ ተቋማት በርካታ ናቸው፡፡

ማንኛውም ሰው ከሚዲያዎች መረጃ የማግነት መብቱ የተረጋገጠ በመሆኑ የጋዜጠኞችም መረጃ የማግኘት መብት አብሮ መከበር መቻል አለበት፡፡ የመረጃ ተደራሽነት ከተረጋገጠ ጋዜጠኞች ትክክለኛ መረጃ ለማህበረሰቡ ማድረስ ይችላሉ፡፡ በመንግስት ተቋማት ያለውን የመረጃ ቋት ለጋዜጠኞች ዝግ ባደረግነው ቁጥር ደግሞ የተዛባ መረጃ ለማህበረሰቡ ለማቅረብ ይሀደዳሉ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ለመረጃ ተደራሽነትም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ መንግስት የመረጃ በሮቹን ክፍት ማድረግ አለበት፡፡

ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሲከበር መልካም አስተዳደርን ጨምሮ ሌሎች ሰብአዊ መብቶች መከበር እውን መሆን ይጀምራል፡፡ በመሆኑም ለህጉ መከበር ሁሉም የድርሻውን መወጣት መቻል አለበት፡፡

 


Comments